በሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የምግብ ስርአትና ኒውትሪሽን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ጋር በመተባበር ከክልሉ ፈፃሚ ሴክተሮችና ከወረዳዎች ጋር የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማዊ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና የዘርፉ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት በፕሮግራሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ማነቆዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
የሐረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱረሂም በመድረኩ ላይ እንደገለጹት መድረኩ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምን በዝርዝር በመገምገም፣ በጀትን በአግባቡ በመጠቀም በቀጣዩ 2019 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያለመ ነው።
የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ዋና ዓላማ ጤናማና አምራች ዜጎችን ማፍራት በመሆኑ ለውጤታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የምግብና ስርዓተ-ምግብ እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍም በቀጣይ ትውልድ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የምግብ ስርዓትና ኒውትሪሽን አማካሪ የሆኑት አቶ አብዱናስር አህመድ በበኩላቸው፤ የፕሮግራሙ ውጤት የሚበረታታ ቢሆንም የሀብት አጠቃቀምን በማቀናጀትና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች በበጀት ዓመቱ የተከናወነውን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የሕጻናትን መቀንጨር ችግር ለመቅረፍና የስርዓተ-ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል ከስድስት ሴክተሮች እና ከ5 ወረዳዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ ተከናውኗል።
በትምህርት ተቋማት በኩል ስለ ስርዓተ-ምግብ የተሰጡ ግንዛቤዎች የህብረተሰቡንና የተማሪዎችን የአመጋገብ ባህል ለመቀየር አወንታዊ ሚና መጫወቱ የተመለከተ ሲሆን፤ ይህም ህጻናት በትምህርታቸው ላይ ንቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ከመርዳቱ በላይ፣ ጤናማ ትውልድ ለመቅረጽ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተገልጿል።
በተያያዥም አርሶ አደሩና የከተማ ነዋሪዎች በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ መደረጉ የቤተሰብን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ህብረተሰቡ የራሱን የተመጣጠነ ምግብ በራሱ እንዲያመርት በማስቻል ረገድ ትልቅ ስኬት መመዝገቡ ተመላክቷል።
በተጨማሪም በገጠር ወረዳዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት የተሰሩ ስራዎች ለእናቶችና ህጻናት ጤና መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበረከታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በጤና ተቋማት በኩልም የተሰጡ የምክር-ሀሳቦችና የህክምና ድጋፎች የህጻናትንና የነፍሰ-ጡር እናቶችን ጤና ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ ማድረጋቸው ተብራርቷል።
የአመጋገብ እጥረቶችን አስቀድሞ በመለየትና ከሴቶችና ህፃናት ሴክተር ጋር በመቀናጀት እናቶችና ህጻናት የፕሮግራሙ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተስፋ ሰጪ ስራዎች መከናወናቸውም ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ባደረጉት ውይይት፤ በቀጣይ በተለይም በግብርና፣ በትምህርት፣ ጤና፣ ውሃ፣ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች እንዲሁም በማህበራዊ ሴክተሮች እና ፕሮግራሙ በሚተገበርባቸው ወረዳዎች መካከል ያለው የጋራ ቅንጅት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም በሀረሪ ክልል በ5 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነፍሰጡርና አጥቢ እናቶችና እድሜአቸው ከ5 አመት በታች ያሉ ህፃናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል ትኩረቱን አድርጎ በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ፕሮግራም መሆኑ ይታወቃል። 







